ስለ ቤተ ክርስቲያናችን

እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት...
"በዚህ ስፍራ የሚመጡና ወደ መንግስቱ የሚጨመሩ ገና ብዙ ሰዎች አሉ"

"ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና"
ቲቶ 2:11

ፀጋ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በ1985 ዓም ከአስር በማይበልጡ ወጣት ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በአቴንስ ከተማ በቤት ውስጥ የተጀመረ መንፈሳዊ ኅብረት ነበር።

እነዚህ ወጣቶች በጊዜው በሃገራችን ከነበረው ሁኔታ ተሰደው የወጡት አብዛኛዎቻቸው ወደ ሰሜን አሜሪካ ጉዞአቸውን ለማቅናት ሲሆን በዚህ በአቴንስም የይለፍ ፈቃድ የሚጠባበቁ ነበሩ።

ከዚህም የተነሳ ስለ ተጀመረው መንፈሳዊ ኅብረት የነበራቸው ዕይታና ሃሳብ ጊዜያዊና ከእነርሱ በስፍራው መቆየት ጋር የተያያዘ ይመስላቸው ነበር።

ይህን አመለካከት ከእነርሱም ቀጥሎ የተተኩት አማኞችም ፤ እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ የሚመጡና ወደ መንግስቱ የሚጨመሩ ገና ብዙ ሰዎች እንዳሉት እንዲሁም ስራውም እንደማያቋርጥ እስከተናገረበት ጊዜ ድረስ የሚጋሩት ሃሳብ ነበር።

ኅብረቱም አድጎ በ1987 በሴንት አንድሪው የጀርመን ቤተክርስቲያን በጥገኝነት በሳምንት ሁለት ቀን እሁድና ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በጉባኤ አገልግሎት መሰጠት ጀመረ።

ይሁንና በቂ አገልጋዮች ካለመኖራቸው የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በሌላ ስፍራ የተሰበኩ የመልዕክት ካሴቶች በጉባኤ የሚሰሙበት ጊዜም ነበር።

ሆኖም በርግጥ ኅብረቱን በአዓላማ የመሰረተውም ሆነ የሚመራው ራሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለነበረ የነበረው መቀባበል መንፈሳዊ ግለትና ማኅበራዊ ኑሮ ከሰው አእምሮ በላይ ነበር። ይህም ለኅብረቱ መዝለቅና ጥንካሬ ታላቅ ኃይል ሆኖ ቆየ።

ኅብረቱ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ወንጌላውያን አማኞችን በአንድነት በአባልነት አቅፎ የያዘ ስለነበር በ1988 ማለቂያ ላይ ሁሉንም የሚያካትት የእምነት አንቀጽ በመተዳደርያ ደንብ ቀርጾ፥ አርቅቆ አወጣ።

አገልግሎቱንም በስፋት ቀጠለ ይሁንና አዲሱ ነገር በዚህ ወቅት አብዛኛው ምዕመን ጌታን የግል አዳኛቸው አድርገው የሚቀበሉት በዚሁ ኅብረት ውስጥ መሆኑ ነብር።

ለኅብረቱ ጌታ የሰጠው ትልቁ ፀጋ ላልዳኑት ወንጌልን መመስከርና የዳኑትም መሰረታዊ የክርስትና ትምህርት አስተምሮ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ከበረቱ በኋላ ጌታ መንገድ ሲከፍትላቸው ወደ ተለያዩ ሃገሮች መሸኘት ነው።

ታዲያ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥም ቁጥሩ ባይታወቅም በሺህ የሚቆጠሩ ነፍሳት በዚህ ኅብረት ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛቸው አድርገው ተቀብለዋል።

አብዛኛዎቹ በአሜሪካ በካናዳና በዚሁ በአውሮፓ ውስጥ ይኖራሉ። ከነዚህ ውስጥም ሙሉ ጊዜአቸውን ለወንጌል ስራ የሰጡና ጌታን በታማኝነትና በትጋት የሚያገለግሉ ወገኖችም ይገኙበታል።

ኅብረቱ ቀላል የማይባል ፈተና ከውጭም ከውስጥም ያጋጠሙት ጊዜ ቢኖርም ጌታ ግን በሁሉ ስለደገፈን እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት የነበረው ጅማሬ አድጎ እስካሁንም ለብዙዎች ከጨለማው ስልጣን የመዳን ምክንያትና ጥላ ለመሆን በቅቷል፣ ወደፊትም በእግዚአብሔር ኃይል ይቀጥላል።

ምንም እንኳን ኅብረቱ አንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን የምትሰጠውን አገልግሎት እንደሚገባ ሲሰጥ ቢኖርም እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ በመንግስት ዕውቅና የነበረው "በግሪክ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ኅብረት" በሚል መጠሪያ ነበር፤ አሁን ግን በዚሁ በ2010 ዓ.ም ማብቂይ ላይ መጠሪያው ተቀይሮ "ፀጋ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን" በሚል ተሰይሞአል።

... ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ...
የዮሐንስ ወንጌል 12:21